ማኅበረሰባዊ ልውጠት[1] (societal Transformation) ማለት የአንድ ማኅበረሰብ የአደረጃጀት፣ የአስተሳሰብ እና የአሠራር ሁኔታ ጥልቀት ባለው መንገድና ረዘም ላለ ጊዜ የሚደረግ መዋቅራዊ ለውጥ ማለት ነው። ማኅበረሰባዊ ልውጠት የአጭር ጊዜ ሪፎርም ወይም የፖሊሲ ማስተካከያ ተግባር ሳይሆን ከአንድ ባህል ወደ ሌላኛው ባህል የሚደረግ ሙሉ ሽግግር ነው። ሽግግሩን ለማሳለጥ የአንበሳ ድርሻ ያላቸው ሞተሮች የሚባሉት ኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) ፣ባህል፣ ቴክኖሎጂና አካባቢያዊ ኀይሎች ናቸው። በማኅበረሰባዊ ልውጠት ጊዜ የሚቀየሩ ዋና ዋና እሳቤዎች የሚከተሉት ናቸው።
- ማኅበራዊ ልማዶችና እሴቶች (Social norms and values) ፡ የማኅበረሰብ እምነቶችና አመለካከቶች የሚቀየሩበት
- ተቋማት (Institutions)፡ቤተሰብ፣ ት/ቤቶች፣ ሃይማኖት፣ መንግሥታዊ ተቋማትና ኢኮኖሚ
- ማኅበራዊ መስተጋብር እና የኀይል መዋቅር (Social relationships and power structures) ፡ ጾታ፣ ብሔር፣ ኀይል(ሥልጣን)
- የማምረቻ ስልት (Modes of production and livelihoods) ፡ከግብርና ስልተ ምርት ወደ ኢንዱስትሪ፣ ከኢንዱስትሪ ወደ ዕውቀት መር ምጣኔ ሀብት ሽግግር ማድረግ።
3.1.1. ዋና ዋና የማኅበረሰባዊ ልውጠት ሞተሮች
1.3.1. ምጣኔ ሀብት ልውጠት (Economic Transformation)
ትልቊ የማኅበሰብ ልውጠት ተብሎ ከሚወሰዱ ሞተሮች መካከል አንዱ የምጣኔ ሀብት ልውጠት ነው። የምጣኔ ሀብት ልውጠት የሚያስከትላቸው ለውጦች
- ከእጅ ወደ አፍ ከሆነው ስልተ ምርት ወደ ኢንዱስትሪ መር ስልተ ምርት መሸጋገር
- ከኢንዱስትሪ መር ስልተ ምርት ወደ ዲጂታል እና ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ሽግግር
- አካባቢያዊ ገደብ ወደ ዓለም ዐቀፍ ገቢያ ተሳታፊነት
እነዚህ ልውጦች በቅጥር፣ በማኅበረሰብ መድብ፣ በሀብት ክፍፍልና በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ በማሳደር በአዲስ መልክ እንዲተረጐም የማድረግ ኀይል አላቸው።
1.3.2. ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ለውጥ (Political and Governance Changes)
በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ውስጥ ንቊ ተሳታፍ ማኅበረሰብና መፍጠርና የተቋማት ግንባታ የፖለቲካና የአስተዳደር ለውጥ ዋንኛ ምሶሶዎች ናቸው። በሕዝብና በመንግሥት መካከል ግልጸኝነት ሲፈጠር፣ ሕዝብ መንግሥታዊ ሥርዐቶችና የለውጥ አጀንዳዎችን የራሱ አድርጐ ሲቀበል እንዲሁም በውሳኔዎች ላይ በንቃት ሲሳተፍ የፖለቲካና የአስተዳደር ለውጥ ያመጣል።
1.3.3. የባሕልና የእሳቤ መቀየር (Cultural and Ideological Shifts)
የተለመዱ እምነቶች፣ ልምምዶችና አስተሳሰቦች አንድ ማኅበረሰብ የሚኖርበትን ዓለም የሚገነዘቡበትን ሁኔታ ይወስናል። ብዙውን ጊዜ የባሕል ለውጥ የሚከሰተው ሕዝቡ ልምምዶችን መጠየቅና መፈተሽ ሲጀምር ነው። የነበረውን ሥርዐት በወጒ የማይፈትሽ፣ ሁልጊዜ ያለፈውን ብቻ የሚያደንቅ፣ ባሕል ከጊዜ ጋር አብሮ እያደገ የሚሄድ ሕያው ሂደት ሳይሆን እንደ ሐውልት ባለበት ተተክሎ የሚቀር ነገር አድርጐ የሚያስብ ማኅበረሰብ ባለበት አካባቢ ለውጥ ማሰብ ያስቸግራል። የለውጥ ተግዳሮትም (change resistance) ከፍተኛ ነው። የባሕል ለውጥ ሂደታዊና ጊዜ የሚፈልግ ቢሆንም ውጤታማነት ግን ከፍ ያለ ነው።
1.3.4. የቴክኖሎጂ ለውጥ (Technological Change)
ቴክኖሎጂ የማኅበረሰብን ለውጥ ከሚያፋጥኑ መሣሪያዎች መካከል አንዱና ዋንኛው ነው። ለውጥን የሚያፋጥነው የሰዎችን የተግባቦት፣ የሥራና መስተጋብርን በመቀየር ነው። ለምሳሌ
- የማተሚያ ማሽን በመፈጠሩ ዓለም ላይ ያለውን የትምህርትና የሃይማኖት ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲካሄደ አድርጓል።
- ኢንተርኔትና ማኅበራዊ ሚዲያ መፈጠር የማኅበረሰብን ግንኙነትና የተግባቦት ባሕልን በመሠረታዊነት ቀይሯል።
- ዲጂታል ቴክኖሎጂ አስተዳደራዊ ሥራዎችን፣ ትምህርትና የአገልግሎት አሰጣጥን ቀይሯል።
1.3.5. አካባቢያዊና ሥነ-ሕዝባዊ ለውጦች
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሀብት እጥረት፣ የሕዝብ ቊጥር ዕድገት፣ ከተሜነት እና ስደት ማኅበራዊ ለውጥን ሊያስከትል ይችላል። በዚህ ረገድ ማኅበረሰባዊ ለውጦች
- የማኅበረሰብ አሰፋፈር ሁኔታ (ከገጠር ወደ ከተማ መፍለስ) ሊቀይር ይቻላል፣
- የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ (ከግብርና ወደ ንግድ)
- ማኅበራዊ ፖሊሲዎች (የጤና፣ የትምህርት፣ ወዘተ. . .)
ከላይ እንደተገለጸው እንደ ኮንሶ ያለን የተፈጥሮ ሀብት በጣም ውስን ነው። በዚህ ላይ ተራራማና ለእርሻ ሥራ ምቹ ያልሆኑ አካባቢዎች ይበዛሉ። በዚህ ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ቊጥር ያለ በመሆኑ አካባቢው ይኸንን ሕዝብ የማስተናገድ ዐቅሙ ዝቅተኛ ነው። ከተሠራበት የሕዝብ ቊጥር ችግር ሳይሆን ሀብት ሊሆን ይችላል። እንዲያውም እንደ ኮንሶ ያለን ትልቊ ሀብት የሰው ሀብት ነው። ወደ ውጪ ገቢያ የሚቀርብ ምርት ተመሳሳይ ከሆኑ የዓለም ዐቅፍ ምርቶች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን በትጋት እንደሚሠራ ሁሉ ዜጎችን ብቁና ተወዳዳሪ አድርጎ በዓለም ዐቀፉ የሥራ ገቢያ ላይ መቅረብ እንዲችሉ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው።
በዚህ መሠረት ኮልሜ ውስጥ ያለውን ሕዝብ በሁለት ጎራ መድበን ማየት እንችላለን። አንደኛው ወጣቱ ትውልድ ሲሆን ሁለተኛው ነባሩ ትውልድ ነው። ውጣቱ ትውልድ በቂ ዕውቀትና ክህሎት አስታጥቆ ለዓለም ዐቀፍ ገቢያ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ነባሩ ትውልድ ደግሞ ቀድሞ በሚሠራው ሥራ ላይ በቂ የሆን ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖረው በየጊዜው ሙያዊ ድጋፎች እየተደረጒለት ዐቅሙን እንዲያሻሽል ይደረጋል። ስለዚህ ከላይ ለተዘረዘሩት ችግሮች የሚነደፉ መፍትሔ ስልቶችን ይኸንን ከግንዛቤ ያስገባ ነው። ወደ እውቀት መር ምጣኔ ሀብት ለመሸጋገር ቀጥሎ በተዘረዘሩ የሥራ ዘርፎች ላይ ትኲረት ማድረግ ያስፈልጋል።
- ትምህርትና ተከፋይ ተቀጣሪነት (Education & Employment)
- ግብርና (Agriculture)
- ንግድ (Business)
- ቱሪዝም (Tourism)
[1] ማኅበረሰባዊ ልጠት (Societal Transformation) እና ማኅበራዊ ልውጠት (Social Transformation) መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ ያሻል። ማኅበረሰባዊ ልውጠት ሁለንተናዊና መዋቅራዊ ለውጥን የሚያመለክት ሲሆን ማኅበራዊ ልውጠት ቀለል ያለና የማኅበረሰብ ግንኙነቶችና መስተጋብሮች ለውጥ ላይ የሚያተኲር ነው።





