የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፪)

የተቋማት ግንባታ ምንነት

ድርጅቶች ወደ ተቋም ደረጃ አድገው ዘመናትን ተሻግረው በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካል መሆኑ እንዲችሉ በተጠና መንገድ መገንባት አለባቸው። የተቋማት ግንባት የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። ከዘመን ጋር አብረው የሚቀየሩ ሳይሆኑ በተለያዩ ሁኔታዎችና የፖለቲካ ሥርዐቶች ለውጥ እንኳን የማይበገሩ ሁሌ ማንነታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተቋማት ግንባታ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ሃይማኖት ዘመናትን የዘለቊት በተቋም ደረጃ ስለተገነቡ ነው። በተቃራኒ በአገራጅን እያንዳንዱ ድርጅት መንግሥት በተቀየረ ቊጥር እንደ አዲስ መልክ የሚደራጀው በተቋም ደረጃ ስላልተገነባ ነው። እንደ ምሳሌ የአገር መከላከያ ተቋም መመልከት እንችላለን። የደርግ ሥርዐት ሲወድቅ ተቋሙ ፈርሷል፣ ኢሕአዴግም የራሱን ለመገንባት ሞክሮ ነበር፣ ሆኖም ብልጽግና ሲመጣ በአዲስ መልክ እንደገና እያደራጀ እንደሆነ ይታወቃል። ይኸ የሚያሳየው ድርጅቶቹ በተቋም ደረጃ ባለመገንባታቸው በየዘመናቱ ለመለዋወጥ ተገድደዋል። ተቋማት የተመሠረቱበትን ዓላማና ግብ በመምሰል ለመርህ መገዛት ይኖርባቸው እንጂ ከፖለቲካ ሥርዐቶችና ከግለሰቦች ፍላጎቶች ጋር መቀያየር አይኖርባቸው። መርሆች አይለዋወጡም።

ጠንካራ ተቋማት ያላት አገር በመሪዎች ድካም ወይም የግል ፍላጎት፣ በሥርዐቶች ለውጥ አይቀያየርም። አሜሪካን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። አሜሪካ ጠንካራ ተቋማት ያላት አገር ናት። የአመሪካ ተቋማት አብዛኞቹ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠሩ ስለሆኑ ጠንካራ ባህልና እሴት ገንብተዋል። ዛሬ እንደ ትራምፕ ያሉ አወዛጋቢ መሪዎች እንኳን ወደ ሥልጣን ሲመጡ በአገሪቱ ላይ ያለው ተጽዕኖ ትንሽ ይሆናል። ምክንያቱም ብዙ የተሳሳቱ ውሳኔዎቹ በጠንካራ ተቋማቱ ውድቅ ስለሚደረግበት።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት ግን ከሚፈተናቸው ነገሮች መካከል አንዱ የተቋማት አለመፈጠር ነው። ተቋማት ግለሰቦችን የሚያገለግሉ ደካማ ሥርዐቶች ናቸው። ወይም ብር ያለው ሁሉ እንደ ልቡ የሚዘውራቸው ናቸው።

በወረዳ ላይ ያሉ የመንግሥት ድርጅቶች ከፖለቲካ ጋር ብዙ መስተጋብር ስለማይኖራቸው(ሊኖራቸውም ስለማይገባ) በሥርዐቶች ለውጥ የሚፈርሱ ሳይሆኑ እንዳሉ መቀጠል እንዲችሉ ወይም በመጠነኛ ማስተካከያዎች ብቻ መቀጠል እንዲችሉ ለማስቻል በተቋም ደረጃ ሊገነቡ ይገባል። የወረዳና የቀበሌ ተቋማት ትልቁ ተልእኳቸው ፖለቲካ ሳይሆን ሥራ ነው። አገሪቱ ውስጥ የተቀረጹ ፖሊሲዎች የሚተገበሩበት ቦታ ነው። ለውጦችን ወደ መሬት የሚያወርዱት እነዚህ ተቋማት ናቸው።

የተቋም ግንባት ማለት አዲስ ድርጅት ፈጥሮ ማጠናከር ወይም የነበረውን ድርጅትና የአሠራር ሥርዐቱን ሪፎርም በማድረግና በማኅበረሰብ ውስጥ አንዳች ተጽዕኖ መፍጠር እንዲችሉ ማስቻል ማለት ነው። ድርጅቶች በማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ የአጭር ጊዜ ወይም የረጅም ጊዜ ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ በትጋት መሥራትና የጊዜን ፈተና መቋቋም እንዲችሉ ማስቻል የተቋም ግንባት አካል ነው። ተቋም ማለት ሕብረተሰቡ የኔ ነው የሚለው ድርጅት ማለት ነው። ተቋማት ተፈጠሩ የሚባሉ ተገማች የሆነና በአብዛኛው ሕብረተሰብ ዘንድ ተቀራራቢ የሆነ የማንነት መገለጫ መፍጠር ሲችሉ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ጤና ጣቢያ ሲሄድ ምንድን ነው ወደ አእምሮው የሚመጣው? ብዙ ሰልፍ? የሠራተኞቹ ማመናጨቅ? ወይስ የሚያዝን፣ የሚንከባከብና ጭንቀታቸውን የሚያቅሉ ሠራተኞች? እንደዚህ ዐይነት እምነቶች በድግግሞሽ የሚፈጠሩ ናቸው። አንዱ ሠራተኛ ጎበ፣ ሌላኛው የሚያመናጭቅ ከሆነ ያ ድርጅት በተቋም ድረጃ አልተገነባም ማለት ነው። ተቋም ተገነባ የሚባለው የግል ባህሪያት በተቋሙ የሙያ ሥነ-ምግባር (professional ethics) ሕጎች ሲዋጡ፣ የግል ስሜቶች በባለ ጒዳዮች ላይ ሳይንጸባረቊ ሲቀሩ ነው። ወጥነት የተቋማት መገለጫ ነው። ተቋሙን የማይመጥኑ የግል ባህሪያት የማይታገሱበት፣ ሁሉም ሠራተና ተቀራራቢ የሆን ባህሪይ ማሳየት ሲችሉ ተቋሙ ተገንብቷል ማለት እንችላለን። ለምሳሌ ባንክ ስትሄዱ ምን ዓይነት መስተንግዶ ታገኛላችሁ? ከንግድ ባንክ ውጪ አብዛኞቹ የግል ባንኮች ሠራተኞቻቸውን በተገቢ ክብር ያስተናግዳሉ። ይኸ ማለት እነዚህ ሠራተኞቹ ሕይወት አልጋ በአልጋ ስለሆነችላቸው ሁሌ ደስተኞች ናቸው ማለት አይደለም። እነሱም እንደማንኛውም ሰው የራሳቸው የሕይወት ውጣ ውረዶች አላቸው፣ እንደ ማንኛውም ሰው የማይመቻቸው የሰው ባህሪይ ሊገጥማቸው ይችላል፣ የሚያናድዳቸውም ደንበኛ ሊገጥማቸው ይችላል። ነገር ግን የራሳቸው ጒዳይ ከተቋሙ እሴት በታች ስለሆነ ይሸፍኑታል። ተቋም ማለት እንደዚህ ነው።

በገጠር ቀበሌያት ያሉ እንደነ ማዘጋጃ ቤቶች፣ የቀበሌ አስተዳደሮች ወይም ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ የሀብት እጥረት፣ የማይመቹ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጦች፣ የሥነ-ሕዝብ ለውጥ ወዘተ. . . ለመቅረፍ የሚረዱ አሠራሮችና መዋቅሮችን መዘርጋት ይኖርባቸዋል። እነዚህ የማኅበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት በድርጅት ደረጃ ብቻ ተቋቁሞ መፍትሔ ለማምጣት መሞከር አይቻልም። ይልቊን እሴቶችን መፍጠር፣ ዐቅም መገንባትና ከአካባቢ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ቀጣይነት ያለውና የሚታመን ተቋም ሆኖ መገኘትን ይፈልጋል። የተቋም ግንባት ሥራ የማኅበረሰብ ዕድገትን ያሸጋግራል። የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ወደ ሕዝብ ሲቀርቡ በተሻለ ቊመና ላይ ሆነው በማኅበረሰቡ እምነት የሚጣልባቸው ሲሆኑ ቀስ በቀስ የዜጎችን ሕይወት የተሻለ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአመለካከታቸው ላይ አዎንታዊ ትጽዕኖ ስለሚያሳድር የሕብረተሰብ ሊወጥ ያመጣል። የዘመናዊነት አንዱ መገለጫ ጠንካራ ተቋማት ነው።

የተቋማት ግንባታ አዲስ ወይም የነበሩ ድርጅቶችን ወደ ተቋም ደረጃ ለማሳደ ማቀድ፣ ማወቀር (structure), ወይም መምራትን የሚያካትት ሲሆን ዓላማውም፦

    የእሴት፣ የተግባር ወይም የቴክኖሎጂ ለውጥ እንዲኖር ማድረግ

    አዳዲስ የሥራ ባህሎችንና አሠራሮችን ማስተዋወቅ

የተቋማት ግንባታ ትኲረት የሚያደርገው የማቀድ፣ የማደራጀት፣ የመተግበር የመቆጣጠርና የመገምገም  ዐቅም ማዳደግ ነው። በተቋም ደረጃ እራሱን ያደራጀ ድርጅት የተሰጠውን ኀላፊነት ያለ ማንም አነሣሺነት ወይም በትንሽ ድጋፍ ብቻ በራሱ መንገድ አቅዶ፣ ተግብሮ አፈጻጸሙን መገምገም ይችላል። ተቋማት ካልተደራጁ እያንዳንዱ ተግባራት በብዙ የሰው ኀይል ተደግፎ እንኳን ግብ ሊመታ አይችልም። ምክንያቱም ተግባሩን የራሴ ነው ብሎ በባለቤትነት የሚቀበል አካል ስለሌለ። ተግባሩ ሲወድቅም በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆን ሰውም አይኖርም፣ ወይም ሊደግፍ የሄደ አመራር ሊወቀስ ይችላል። ይኸ ማለት ለደቦ ሥራ ሄዶ እንደሚወቀስ ሰው ማለት ነው። ነገር ግን መወቀስ ያለበት ተቋሙ ራሱ ነው።

ከሁሉም በላይ ተቋማት ካልተደራጁ አፈጻጸማቸው በሠራተኞች ድካምና ጥናካረ ላይ ይመሠረታል። አንድ ጎበዝ ሠራተኛ ሲያገኝ የተወሰነ የመንቀሳቀስ አዝማሚያ ሊያሳይ ይችላል። ያ ጎበዝ ሠራተኛ ሲተው ሁሉም ነገር አብሮ ይቆማል። በሰው ላይ ጥገኛ የሆነ ድርጅት ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪ በሥርዐት ያልተደራጅ ተቋም ሠራተኞቹ ያለ ውጤት በሥራ የተወጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሁሉም ሰው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ሊባትል ይችላል፣ ውጤቱ ሲታይ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም።

ተቋማትን ማደረጀት ሌላኛው ጥቅሙ ብልሹ አሠራሮችን ለመፋለም ይረዳል። ግልጽ የሆኑ የአሠራር ሥርዐቶች ከተዘረጒ ስህተት ቢፈጠር እንኳን ቶሎ ለማግኘት ይረዳል። ደካማ ተቋማት የብልሹ አሠራር መፈልፈያ ዋሻዎች ናቸው። ሁልጊዜ የሕብረተሰብ እሮሮ ማሰሚያ ቦታዎች ይሆናሉ። ከዓመት ዓመት ምንም ለውጥ ሳያሳዩ ባሉበት እየረገጡ ይሄዳሉ። ተቋም ከተገነባ ግን የቱ ጋር መሻሻል እንዳለበት በቃሉ ስለሚታይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ይሄዳል።

ይቀጥላል

  • Related Posts

    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፫)

    የተቋም ግንባታ ሥራዎች አገራችን ኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዐተ መንግሥት ቅርጽ የምትከተል በመሆኗ መዋቅራዊ አደረጃጀቱ ተዋረዳዊ (Hierarchical) ነው። ተዋረዱ ከላይ ወደ ታች ሲዘረዘር ፈዴራል፣ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ ናቸው። ሥልጣንና ተግባራት…

    ማንበብ ይቀጥሉ

    Continue reading
    የተቋማት ግንባታ

    የተቋም ግንባታ መሠረታውያን መግቢያ የምንገኝበት ዘመን በጣም ፈጣንና ተለዋዋጭ ነው። በየጊዜው አዳዲስ ችግሮችን እናስተናግዳለን። የሥራ ጫናው ካለው የሠራተኛ ብዛት አንጻር ሲታይ የት የለሌ ነው። ከላይኛው የመንግሥት መዋቅር የሚወርዱ ተልእኮዎች ሁሉ…

    ማንበብ ይቀጥሉ

    Continue reading

    Leave a Reply

    Your email address will not be published. Required fields are marked *

    You Missed

    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፫)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 130 views
    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፫)

    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፪)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 113 views
    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፪)

    የተቋማት ግንባታ

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 93 views
    የተቋማት ግንባታ

    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፫)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 79 views
    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፫)

    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፪)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 133 views
    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፪)

    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፩)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 88 views
    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፩)