የሰላም ግንባታ ምንነት
ወደ ሰላም ግንባታ ከመሄዳችን በፊት ‘ሰላም’ የሚለውን ቃል በአግባቡ መተርጐም ያስፈልጋል።
ሰላም ምድን ነው?
በሰው ልጅ ሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው እሴቶች መካከል አንዱ ሰላም ነው። ሰላም ከሰው ልጅ አልፎ የፍጥረታት ሁሉ የመኖር ዋስትና ነው። ሰው ከወገኑ ጋር ሲገናኝ የሚጠይቀው ሀብት፣ ደስታ፣ ፍቅር፣ ወዘት አይደለም። ሰላምን ነው። ይኸ የሚያሳየው ሰላም ለሰው ልጅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ነው። ግን ሰላም ምንድን ነው? ሰላም በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ የምንጠራው ቃል ቢሆንም ትርጒሙና ምንነቱን የሚረዱት ግን ብዙዎች አይደሉም። ሰላም ምንድን ነው?
ሰላም ሰፊ ትርጒም ያለው ቃል ነው። ለተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ትርጒም ይሰጣል። የቃሉ መነሻ የሴማዊ ቋንቋ ሲሆን በአራማይ shalam, በሕብርው ቋንቋ ሻሎም፣ በአረቢኛ salam፣ በአማርኛ ‘ሰላም’ የሚል ቃል ሲሆን በእንግሊዝኛ peace የሚለውን ቃል ይይዛል። ትክክለኛ ትርጉሞ የጦርነት መጥፋት ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የሆነ ሐሳብ ይይዛል። ይኸኛውንና የሚመጣውንም ዓለም የሚያካትት ውጫዊና ውስጣዊ ሁለንተናዊ ቋሚ እረፍትን ያመለክታል[1]። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ኀላፊዎች ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ የሚገባ ሰብአዊ ክብር(diginity)፣ ሁለንተናዊ ደህነነት (Wellbing) ነው። በሌላ መንገድ ሰላም ማለት ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን (social relations) ጤናማ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ማኅበራዊ እሴት ማለት ነው። ሰላም ከሌላ ሰው ጥቃት ይደርስብኛል ብሎ አለመፍራትንም ያጠቃልላል። ሰላም ከፍርሃት ነጻ የሆነ ሕይወት ነው። ሰላም ሲኖር ሰው ፍርሃት ይጠፋል።
የሰላም ዓይነቶች
ሰላም አሉታዊና (negative) አዎንታዊ (positive) ብሎ መከፋፈል የተለመደ ነው።
አሉታዊ ሰላም የሚባለው ግጭት ወይም ጦርነት አለመኖር አሊያም የግጭት ወይም የጦርነት ፍርሃት አለመኖር ማለት ነው።
አዎንታዊ ሰላም ደግሞ በማኅበረሰብ ውስጥ ስለ ሰላም አስተሳሰብ (attitude) ሲፈጠር፣ የሰላም ተቋማት (institutions) ሲኖሩ ወይም ሰላምን የሚያስጠብቊ ማኅበራዊ ወይም መንግሥታዊ መዋሮች(structure) ሲኖሩ የሚፈጠር የሰላም ዓይነት ነው። ይህ ከፍ ያለ የሰላም ደረጃ የሚያሳይ ነው። አንድ ማኅበረሰብ በአሉታዊ ሰላም ብቻ መኖር አይችልም። ምክንያቱም በየትኛውም ሰዓት ግጭት ወይም ጦርነት ሊነሣ ስለሚችል። ማኅበረሰቡ ሰለ ሰላም ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ከሆነ፣ ሰላምን የሚያስጠብቊ ተቋማት ካልተገነቡ በጥቃቅን ግጭቶችም ወደ ጥቃትና[2] (violence) ጦርነት ሊያመራ ይችላል። አዎንታዊ ሰላም ለመገንባት ማኅበረሰባው ሥነ-ልቦናና በዓላማ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። ሰላም በራሱ አንዱ ልማት መሆኑን የተገነዘበ ማኅበረሰብ በየትኛውም ዋጋ ሰላምን ያስቀድማል። መጥፎ ሰላም ወይም ቅዱስ ጦርነት እንደሌለ ይረዳል።
የሰላም ግንባታ
የሰላም ግንባታ እንደማኛውም ነገር ግንባታ ጥረት፣ ሀብትና ጊዜ የሚጠይቅ ቀጣይነት ያለው ሥራ ነው። በተለይ በግጭት ውስጥ ለቈዩ አካባቢዎች የሰላም ግንባት የሚፈልገው ጥረት ከፍተኛ ነው። የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፉ የነበሩት ኮፊ አናን በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ‘ሰላም መፍጠርና ለግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በከፍተኛ ደረጃ የሁለቱም ወገኞች ከፍተኛ ቆራጥነትና ያልተለመድ ድፍረት የሚጠይቅ ሥራ ነው።’
የሰላም ግንባታ ስንል በግጭት ውስጥ የቆዩ ማኅበረሰቦችን የማከምና ወደ ጤናማ ማኅበራዊ መስተጋብር የመመለስ ሥራ ነው። ሂደቱም እውነትን በመያዝ የግጭቱ ዋና ምንጭ/ምንጮችን መለየት፣ ለተፈጠሩ ጒዳቶች ተገቢ የሆነ ዕውቅናና የማገገሚያ ፍትሕ (restorative justice) መፍጠር ወይም የተጎዱትን መካስ፣ ማኅበራዊ እርቆችን (reconsilation) ማካሄድና ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር ወዘተ. . . ያጠቃልላል። የሰላም ግንባታ ሥራ በጣም ፈታኝና የሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ጥረትና ትዕግሥት የሚጠይቅ ከመሆኑም ባሻገር ቀጣይነት ያለው ሥራ በመሆኑ በአንድ ወቅት ግርግር ብቻ የሚፈጠር አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ሰላም ለመገንባት የሚያስፈልጒ ምርጫዎች
- እውነት
- ከ retributive justice ይልቅ restorative justiceን መምረጥ (በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ሥራ፣ እነ ስብሐት ነጋ፣ ጃዋር መሐመድ፣ ዘመኔ ካሴ ከእስር የተፈቱበት መንገድ፣ እነ ጌታቸው ረዳ ወደ ሥልጣን የመጡበት ምክንያት
- ግለሰባዊ ፈውስ (በቀውስ ውስጥ ያለፉ፣ ሰው የሞተባቸው፣ ንብረት የወደመባቸው ግለሰቦችን ማቋቋም፣ ማጽናናትና የአእምሮአቸው ጤንነት እንዲመለስ ማድረግ
- የሰላም ሠራተኞች (peace builders) መፍጠር
[1] ሰለሞን ጥላሁን፡ ዐብረን ሰው እንሁን፣ የግጭት ልውጠት መሠረታውያን (2013 ዓ.ም)፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፣ ገጽ 245
[2] ጥቃቶች አካላዊ ወይም አእምሮአዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ጥቃቶች በግለሰቦች፣ በቡድኖች ወይም በመዋቅር ሊከሰት ይችላል። አንድ መንግሥታዊ ወይም መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም አንዱን ቡድን ደግፎ ሌላኛውን ሊጎዳ ይችላል፣ እሱም እንደ ጥቃት የሚቆጠር ሲሆን ተበድያለሁ ወይም ፍትሕ ተነፍግያለሁ ያለው አካል ወይም ቡድን እንደተጠቃ ይቆጥራል።




