የወረዳዉ አጠቃላይ ገጽታ
የኮልሜ ወረዳ በኮንሶ ዞን ከሚገኙ 4 ወረዳዎች ውስጥ አንዱ ነዉ፡፡ ወረዳዉ በ5016’15” እስከ በ5021′20′′ ሰሜን ላቲትዩድ እና በ 37020′ 15′′ እና 37026’49′′ ምስራቅ ሎንጊትዩድ መሥመሮች ዉስጥ የሚገኝ ሲሆን አዋሳኞቹ በደቡብ የቦራና ዞን(ቴልቴሌ ወረዳ)፣በምዕራብ የደቡብ ኦሞ ዞን (በና ፀማይ ወረዳ)፣ በሰሜን የኧሌ ዞን (ኮላንጎ ዙሪያ ወረዳ) እንዲሁም በምስራቅ ከና ወረዳ እና ካራት ዙሪያ ወረዳ ናቸዉ፡፡ ወረዳዉ ከባህር ጠለል በላይ ከ501—2000 ሜትር ከፍታ ያላቸዉን ሥፍራዎች የሚሸፍኑት ሲሆን አየር ንብረቱም 70% ደረቅ ቆላማ፣ 30% ደግሞ ወይና ደጋ እንደሆነና አመታዊ አማካይ የሙቀቱ መጠን ከ17.8 ዲግር ሴንትግሬድ እስከ 28.6 ይደርሳል፡፡
የወረዳዉ ቆዳ ስፋት 454.3 ኪ. ሜ2 ሲሆን ፡፡ የሕዝብ ሥርጭት/አሰፋፈር/ ከቦታ ቦታ የሚለያይ ሲሆን ጥግግቱ በስኩየር ኪ.ሜትር 106 ሰው ነው፡
ወረዳዊ ተቋማዊ ገፅታ
- ማህበራዊ ሁኔታዎች
በጤናውም ረገድ ኅብረተሰቡ ጤናዉ ተጠብቆ አምራች ዜጋ እንዲሆን በሁሉም የቀበሌ አካባቢዎች ከህብረተሰቡ አሰፋፈርና ከአካባቢዉ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ ጤና ጣቢያዎች ፣ ጤና ኬላዎች በመገንባትና ቁጥር ያላቸው የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት የጤና አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል፡፡
2. ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች
የወረዳዉ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በግብርና ላይ ሲሆን 86 በመቶ የሚገመተው የሰው ኃይል በግብርና የሚተዳደር ሲሆን 14 በመቶ በንግድ፣ ኢንዱስትሪና በልዩ ልዩ አገልግሎት ሰጭ ተግባራት እንደተሰማራ ይገመታል፡፡ በወረዳዉ የሚኖረው የገጠር ህዝብ ውስጥም በሰብል ልማት፣ በእንስሳት ዕርባታና በጥምር እርሻ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡
ዞናችን ለግብርና ልማት ተስማሚ የሆነ የተለያየ የአየር ንብረት፣ የአፈር ዓይነት፣ ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል መሬትና መጠነኛ የሆነ የውሃ ሃብት ያለው ቢሆንም በአብዛኛው የተመሠረተው የዝናብ ውሃን በመጠቀም ላይ እንደሆነ ይታመናል፡፡
በጨማሪም የውጭ ምንዛሬና የአርሶ አደሩን ገቢ በማሰደጉ ረገድ ከቡና በተጨማሪ የገቢያችንን ሁኔታ ቀጣይና አስተማማኝ በማድረግ በአገር ውስጥና በውጪ ገበያ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ የጥራጥሬ፣ የፍራፍሬ፣ የቅባትና የቅመማ ቅመም ምርቶችን ለማስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በወረዳችን ያሉት ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሀብትነት የተመዘገቡትን የእርከን ሥራ፣ የአፈርና የውሃ ጥበቃ እና ልማት ሥራ፣ ባህላዊ የቤት አሰራር ለመጎበኘት በዓመት በርካታ ቱሪስቶች ወደ ወረዳችን እንድጎርፉ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
3. ቴክኖሎጂያዊ ሁኔታ
ፈጣንና ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥና ግንኙነት እንዲኖር ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡ በዚሁም መሠረት በወረዳችን የኢኮቴ አጠቃቀም ለማጠናከር ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ የሞባይል መስመር ተጠቃሚዎች፣ መደበኛ ስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት መድረሳቸው ከወረዳዉ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ጋር እየተሠራ ይገኛል፡፡
4. ፖለቲካዊና የመልካም አስተዳደር ገጽታዎች
መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መዘርጋት አማራጭ የሌለው ቁልፍ ተግባር መሆኑ በወረዳዉ መንግሥት ታምኖበት ለተግባራዊነቱም የተለያዩ አደረጃጀቶችንና አሠራሮችን በመንደፍ በሁሉም የአስተዳደር እርከን ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የወረዳዉን ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያረጋገጠ አመቺና አሣታፊ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ተዘርግቶ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስጠበቅ፣ ልማትና ዕድገትን ለማምጣትና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል መንግሥታዊ መዋቅር ማለትም የህግ አውጪ ፣ አስፈፃሚና የዳኝነት አካላትን በማደራጀት የወረዳዉን ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የወረዳዉ መንግሥት የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ፓኬጆችን በመቅረፅ የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሠጣጥን የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ፣ ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተሳትፎ እንዲኖረው እና ግልፀኝነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ለማስፈን እንዲቻል በርካታ ተግባራትን ለምሳሌ የዜጎች ቻርተር በማዘጋጀት ተግባራዊ መደረጉ፣ የቅሬታና የይግባኝ አገልግሎትን ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች መሰራታቸው፣ የለውጥ ሠራዊት መገንባቱና መደራጀቱ፣ በመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች በሥፋት መሰጠታቸውና በየደረጃው የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች በመፈጠራቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተፈቱ ይገኛል፡፡
የፍትህ ሥርዓቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ከማድረግ አኳያም የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ ፓኬጆች ተቀርጸው ተግባራዊ በመደረጋቸው የዳኝነት ሥርዓቱን እና ፖሊሳዊ አገልግሎትን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ የወረዳዉን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር የሚያስችሉ የተለያዩ መንግሥታዊና ህዝባዊ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና አቅማቸውን በማሳደግ በማቀናጀት ወደ ተግባር ማስገባት በመቻሉ የወረዳዉ ሰላምና ፀጥታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ይገኛል፡፡
የኮልሜ ወረዳ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍና ስር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ የአደረጃጀትና የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት በየደረጃው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደረጉ በርካታ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
የኮልሜ ወረዳ ዋና አስተዳደር ጽ/ቤትም በክልሉ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 70 ንዑስ ቁጥር 2 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ተደራጅቶ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ጽ/ቤቱ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ፣ በአስተዳደራዊ፣ በፀጥታና ህዝብ ደህንነት፣ በሕግ ጉዳዮች፣ በበይነ-መንግሥታዊ ግንኙነቶች፣ በመሠረተ-ልማትና በመሳሰሉት ጉዳዮች በዋና አስተዳዳሪ የመደገፍ፣ የማማከር፣ የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብና ዝርዝር ጥናት የማድረግ ሚናውን መወጣት እንዲችል በዕቅድ መመራት አስፈልጎታል፡፡


