የሰላም ግንባታ (ክፍል ፩)

የሰላም ግንባታ መሠረታዊ ሐሳብ

መግቢያ

የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳ[1] ነው ይባላል። ማኅበራዊ እንስሳ የተባለበት ምክንያት ሰው በተፈጥሮ ለብቻ መኖር የሚችል ፍጡር ባለመሆኑ ነው። የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ በሕይወት ለመኖር ከሚያስፈልጒ መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል አንዱ ሕብረት ነው። የአፈጣጠር ታሪክ የሚያትተው የዘፍጥረት መጽሐፍ ሲናገር እግዚአብሔር አዳምን ቀድሞ ከፈጠረ በኋላ ብቸኛ መሆኑን አይቶ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።” ማለቱን ያስነብበናል። ይኸ ሐሳብ የተነገረው ብዙ ፍጥረታት ከተፈጠሩ በኋላ ነው። ከፍጥረታት መካከል ግን ለአዳም አጋር የምትሆን አልነበረችም። ብዙውን ጊዜ ጥቅሱ ለሚጋቡ ሰዎች ሥራ ላይ ይውላል። በርግጥ ሐሳቡ ከአዳምና ሔዋን ግንኙነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለጋብቻ መጠቀሱ ትክክል ነው። ቢሆን ግን መልእክቱ ከዚያ ያለፈ ትርጒም አለው። የሰው አፈጣጠር ብቸኝነትን አይቋቋምም። ለዚህ ነው ዓለማችን ላይ ከፍተኛ ከሆኑ የቅጣት ዓይነቶች ውስጥ አንዱ ሰው ከሰው ነጥሎ ለብቻ ማሰር (solitary Confinement)[2] ተብሎ የሚታመነው። የሰው ልጅ ያለ ሌላኛው ወገኑ መኖር አይችልም። ምንም እንኳን በአንድ ላይ በምንሆንበት ጊዜ ጥቅሙ ባይገባምንም፣ ከሰው ተነጥለን ለመኖር በምንሞክርበት ጊዜ ሰው ለሰው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። ስለዚህ ሰው ለሰው መድኀኒት ነው።

ሰው ማኅበራዊ እንስሳ በመሆኑ በጋር ይኖራል። በጋራ በሚኖርበት ጊዜ በተለያዩ ማኅበራዊ ጒዳዮች ይተሳሰራል። ችግሮቹን በጋር ይጋፈጣል። ደስታዎቹም በጋራ ይካፈላል። የሰው ልጅ ችግሮቹን ለብቻ መቋቋም እንደማይችል ሁሉ ደስታም ለብቻ ማጣጣም አይሆንለትም። ሁሉም ነገር በጋራ ሲሆን ሙሉ ይሆናል። ብቸንነት ግን በሽታ ነው። ታዲያ በሰው ልጆች መካከል ያለው ሕብረት ከቤተሰብ ይጀምርና ወደ ማኅበረሰብ ያድጋል። ማኅበረሰቦች ተያይዘው አገር ይፈጥራሉ። አገራት በተራ ተያይዘው ዓለምን ይፈጥራል። ስለዚህ ትንሹ የሰው ልጆች ሕብረት ቤተሰብ ሲሆኑ ትልቊ ደግሞ ዓለም ነው። ምክንያቱም የሰው ልጆች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች በአጠገቡ ባሉ ሕብረቶች ብቻ የሚፈቱ አይደሉም። ሰው ከጎረቤቱ የተሰነ ነገር ማግኘት ቢችልም በቂ ስለማይሆንለት ወደ ሩቅ ያማትራል። በዚህ ምክንያቱ የሰው ልጆች በፍላጎቶች የተሳሰሩ ናቸው። በተለይ ዛሬ ያለንበት ዘመን ከፍተኛ የትስስር ደረጃ ላይ የደረሰበት ዘመን ላይ ነን። ሉላዊነት (globalization) የምንለው ዓለም በሙሉ በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በንግድ፣ በፖለቲካ ወዘተ. . . መተሳሰሩን የሚያሳይ ቃል ነው። ሕብረቶቹ እየሰፉ ሲሄዱ የባህልና የቋንቋ ልዩነቶች ቢፈጠሩም ሰው በመሆናችን ግን በብዙ ነገር እንተሳሰራለን። እንዲያውም ልዩ ያደርገናል ብለን ከምናስባቸው ምክንያቶች ይልቅ የሚያስተሳስሩን ሰብአዊ ማንነቶች ይበልጣሉ።

ነገር ግን እነዚህ ሰብአዊ መስተጋብሮች(relations) በተለያዩ ምክንያቶች ይሸረሸራሉ። ግንኙነቶቹ ከተሸረሸሩ በኋላ በሰው ልጆች መካከል ያለው ሕብረት ይሻክራል። በመጨረሻም በጥል፣ በግጭትና በጦርነት ይገለጣሉ። ስለዚህ በሰው ልጆች መካከል አንድነትና ሕብረት እንዳለ ሁሉ ግጭቶችና ጦርነቶች የተለመዱ ክስተቶች ናቸው። እነዚህ አሉታዊ ክስተቶች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ዓለም ዐቀፍ ድረስ የሚዘልቊ ናቸው። ቤተሰብም ይጣላል፣ አገራቱም ይጣላሉ። የሰው ልጅ ሕብረት ፈላጊ በመሆኑ የፈለገውን ያህል ቢጣላ በመጨረሻ መታረቊ አይቀርም። ምክንያቱም ሰው በጥል ውስጥ በዘላቂነት መኖር አይችልምና።

ግጭቶችና ጦርነቶች አስከትሎቶቻቸው እጅግ አሉታዊ በመሆናቸው የሰው ልጅ ሰላምን በከፍተኛ ዋጋ መጠበቅ እንዳለበት ተረድቷል። ከዚህ የተነሣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሰላም ጥናት (peace studies) በዩኒቨርሲቲዎች እንደ አንድ የጥናት መስክ መጠናት ጀምሯል። ከመደበኛ ጥናቶች በተጨማሪ በሕብረተሰብ መካከል የሰላም ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋምት የተለያዩ ሥልጠናዎችም እየተሰጡ ይገኛሉ።

እንደ ቀጠናችን[3] ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የሰላም መደፍረሶች ውስጥ ማለፋችን ይታወቃል። የተናጋውን ሰላም ወደ ጤናማ ግኙነት ለመመለስ የተደረጉ ብዙ ጥረቶችም ነበሩ። ሆኖም ግን ከችግሮቹ ሰፋትና ካስከተሉት አሉታዊ ተጽዕኖሮች የተነሣ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ በቊጥጥር ሥር ውለዋል ማለት አይቻልም። እስከ ዛሬ ድረስ መፍትሔ አሁንም በሕብረተሰብ መካከል ስጋት እየፈጠሩ ያሉ ግጭቶች አሉ። ከነዚህ መካከል አንዱ በኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳና በኧሌ ዞን መካከል ያለው ግጭት ነው። ይኸ ግጭት ከተፈጠረበት ጊዜ አንሥት እስከ ዛሬ ድረስ ሁሉንም ወገኞች የሚያግባባ የመፍትሔ ውሳኔ ባለማግኘቱ በየጊዜ እያገረሸ በቀጠናው ላይ ብዙ ውጥረቶችን እየፈጠረ ይገኛል።

ይቀጥላል


[1] የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳ ነው ብሎ በመጀመሪያ የተናገረው ታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ አርስቶትል ነው።

[2] ይህ ዓይነት እስር ቀጥታ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር ስለሚገናኝ በአሁኑ ዘመን አይደገፍም።

[3] በዚህ ሰነደ ላይ ላይ ቀጠና ወይም ቀጠናችን ተብሎ ሲገለጽ በዋናነት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ያሉና በቀድሞው የሰገን ሕዝቦች ዞን ሥር የተደራጁ ዞኖችን ለማመልከት ነው።

  • Related Posts

    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፫)

    የሰላም ግንባታ ምንነት ወደ ሰላም ግንባታ ከመሄዳችን በፊት ‘ሰላም’ የሚለውን ቃል በአግባቡ መተርጐም ያስፈልጋል። ሰላም ምድን ነው? በሰው ልጅ ሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው እሴቶች መካከል አንዱ ሰላም ነው። ሰላም ከሰው…

    ማንበብ ይቀጥሉ

    Continue reading
    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፪)

    የሰላም ግንባታና የሰው ልጅ የትግል ታሪክ ኑሮ ትግል ነው ይላሉ ሰዎች። ሰው ከእናቱ ማኅጸን ወጥቶ ይህችን ዓለም ከተቀላቀለበት ቅጽበት አንሥቶ የመጨረሻ እስትንፋሱን መተንፈስ እስከቻለበት ድረስ በግልም ከሌሎች አቻዎቹ ጋር በመሆንም…

    ማንበብ ይቀጥሉ

    Continue reading

    Leave a Reply

    Your email address will not be published. Required fields are marked *

    You Missed

    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፫)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 131 views
    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፫)

    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፪)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 113 views
    የተቋማት ግንባታ (ክፍል ፪)

    የተቋማት ግንባታ

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 94 views
    የተቋማት ግንባታ

    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፫)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 79 views
    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፫)

    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፪)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 133 views
    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፪)

    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፩)

    • By admin
    • June 27, 2026
    • 89 views
    የሰላም ግንባታ (ክፍል ፩)