ዓላማዎች
ይኸ ጽሑፍ ቀጥሎ ባሉ ርዕሶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ነው።
- የመንግሥት ምንነትና አስፈላጊነትን
- የመንግሥት ዓይነቶችና ባህሪያቸውን
- የኮንሶ ሕዝብና የመንግሥታት ግንኙነት
- የኰልሜ ወረዳ ያለፈባቸው የዕድገት ደረጃዎች
- ወረዳ ከተፈጠረ በኋላ ያለው ሁኔታ
መግቢያ
የሰው ልጅ ለብቻ ተነጥሎ የሚኖር ፍጡር አይደለም። ለዚህ ነው ገና ከጅምሩ በጋራ በአንድ ስፍራ ተሰባስቦ መኖር የጀመረው። ለሰው ልጅ በጋር መቆም ለሕልውናው መሠረት ነው። ለብቻ መቆም ያሰበ ዕለት ወዲው ለተለያዩ አደጋዎች ይጋለጣልና። ነገር ግን በጋራ በአንድ ስፍራ ተሰባስቦ መኖር በራሱ ሌላ ፈተና አለው። እሱም የሰው ልጆች ገደብ የለሽ ፍላጎትና የባህሪይ አለመጣጣም አብሮነቱን ያበላሽበታል። ሁሉም ሰው የፈለገውን ነገር በፈለገው ጊዜና በፈለገው መጠን ለማሳካት በሚሮጥበት ጊዜ የሌሎች ሰዎችን ፍላጎት መደፍጠጡ አይቀርም። አንዱ የሌላውን ፍላጎት በሚሻማት ጊዜ ግጭት ይፈጠራል። ግጭቶች ሲያይሉ ወደማያባራ ጦርነት ይመራል። ከዚህ የተነሣ የሰው ልጅ አብሮ ለመኖር ሲባል ከፍላጎቶቹ ቀነስ በማድረግ ሕግ ማበጀት ጀመረ። ይኸ ሂደት መንግሥት የምንለውን ተቋም ወደ መመሥረት አመራ። ለመሆኑ መንግሥት መንድን ነው?
- የመንግሥት ምንነትና አስፈላጊነት
የሰው ልጅ በዓለም ላይ ከፈጠራቸው አስደናቂ ሥርዐቶች መካከል አንዱ የመንግሥት ሥርዐት ነው። መንግሥት የሚባል ሥርዐት ባይፈጠር የዓለም ሥልጣኔ ባልተፈጠረ ነበር። ያለ መንግሥታዊ ሥርዐት አንድ ማኅበረሰብ በሥርዐት መኖር አይችልም።
የመንግሥት ምንነት
መንግሥት ማለት አንድ አገር ወይም ማኅበረሰብ የሚተዳደርበትና የሚቆጣጠርበት ፖለቲካዊ ሥርዐት ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ መንግሥት ሲባል በሕግና በሥርዐት የሚመራ የማኅበረሰብ ስብስብ ማለት ነው። መንግሥት በሚለው ሥርዐት ውስጥ ሦስት የተለያዩ ኀላፊነት ያላቸው አካላት አሉ። እነሱም ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ ናቸው። የመንግሥት ሥልጣን በነዚህ አካላት መካከል ይከፋፈላል።
መንግሥት ለምን አስፈለግ?
መንግሥት እንዴት እንደተፈጠረ ያብራሩት ምሁራን የመንግሥት አስፈላጊነት ከሰው ልጅ ገደብ የለሽ ፍላጎት የሚፈጥረው ችግር ጋር ያያይዙታል። ይኸንን ለማስረዳት State of nature የሚል ምናባዊ ማኅበረሰብ ያስቀምጣሉ። State of nature ማለት መንግሥት ከመፈጠሩ በፊት የነበረው ምናባዊ ማኅበረሰብ ማለት ነው። መንግሥት የሚባል ተቋም ባይኖር ሕዝብ እንዴት ይኖር ነበር የሚለውን ግንዛቤ ለማግኘት ነው። በ State of nature ሕዝብን የሚያስተዳድር አካል አይኖርም፣ ሕግ አይኖርም፣ ሥርዐት አይኖርም። የሰው ልጅ ባልበዛበትና የሀብት እጥረት ባልተፈጠረበት ጊዜ ሰው ያለ መንግሥት ቢኖር ብዙ ችግር አልነበረውም። ነገር ግን የሕዝብ ቊጥር ሲጨምር፣ የሀብት እጥረት ሲከሰት ያለ መንግስት መኖር እጅግ አደጋች አደረገው። ይኸ የሚሆነው ከሰው ልጅ ፍላጎት የሚነሣ ነው። ሰው ሀብት የማፍራት፣ ሁሉንም የራሱ የማድረግ ያልተገደብ ፍላጎት አለው። ይኸ ያልተገደበ ሀብት የማፍራት ፍላጎት በመጨረሻ ወደማያባራ የእርስ በርስ ግጭት ያመራል። ይህ በምሁራኑ አገላለጽ War of All Against All የሆነበትሥርዓት ይፈጠራል።ያለ መንግሥት ሕይወት በብቸኝነት የተሞላች፣ ድህነት ያቆራቆሳት፣ በጭካኔ የተሞላችና በአጭሩ የምትቀጭ ትሆናለች። ሰው የፈለገውን ያህል ጠንካራ ቢሆን ያለ መንግሥታዊ ሥርዐት ምንም ማድረግ የማይችል ደካማ ፍጥረት ነው። ጠንካራ የተባለ ግዙፉ ሰውዬ በደካማ ሰው ሊጠቃ ይችላል።
በ State of nature ጊዜ ነገን ማሰብ አይቻልም። በማንኛውም ጊዜ የሰው ሕይወት በጒልበተኞች እጅ ልትነጠቅ ትችላለች። ንብረት ማፍራት አይቻልም። አንዱ ያፈራው ሌላኛው ጒልበተኛ መጥቶ ያጠፋዋል ወይም የቀማዋል። የጋራ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አይኖሩም ምክንያቱም ሁሉም የራሱን እንጂ የጋራ ሀብት ስለማያስብ ገንዘብ አያዋጣም። ሀብታምና ድሃ አንድ ላይ መኖር አይቻሉም፣ ምክንያቱም ያንተ ሀብት ሌላ ያጣ ሰው መጥቶ ይወርስብሃል። ሰላም ብትፈልግ አታገኛትም። ወንጀለኛ አይታሰርም፣ ፍትሕ አይረጋገጥም። ሕይወት በጫካ ሕግ (Law of the jungle) ትመራለች። ጒልበተኞች ብቻ የሚኖሩባት ዓለም ይፈጠራል። በሕይወት ለመቆየት ብቸኛ አማራጭ እረፍት በሌለው ጦርነት ውስጥ መቆየት ይጠይቃል፣ ከሁሉም ጋር ጦርነት (War of All Against All) ።
ይኸንን የሚመስል ቀውስ የተሞላበት ሕይወት ለመቀየር መፍትሔው ምንድን ነው?
መፍትሔው መንግሥታዊ ሥርዐት መፍጠር ነው። ሰዎች ካልተገደበ ነፃነታቸው የተወሰነውን ቀንሰው ከሁሉም ዐቅም በላይ የሆነ አካል ይፈጥራሉ። ይህ በሰዎች ስምምነት የተፈጠረ ኀያል አካል መንግሥት ነው። ከሁሉም በላይ የሆነ፣ ሁሉም የሚታዘዝለት፣ ሁሉም የሚያከብረው ሥርዐት ይሆናል። መንግሥት ኀያል ስለሆነ ማንንም ጒልበተኛ የመቅጣት ሥልጣን አለው። ጎበዙ ደካማውን እንዳያጠቃ፣ ሌባ እንዳይሰርቅ፣ የተቆጣ ሁሉ ጠላቴ ነው ያለውን እንዳይገድል መንግሥት ሥርዐት ያስጠብቃል።
መንግሥት ሲኖር ተስፋ አለ። ምክንያቱም ሰዎች ልጅ ሲወልዱ እንደሚያሳድጒ ተስፋ ያደርጋሉ፣ እህል ሲዘሩ ወደራሳቸው ጎተራ እንደሚያስገቡ ተስፋ ያደርጋሉ፣ ንብረት ቢያፈሩ ማንም እንደማይነጥቃቸው ይተማመናሉ። የሞከረ ካለ ሥርዐት የሚያስይዝ አካል ስላለ በሕግ ያስጠይቃሉ።
ስለዚህ መንግሥት ማኅበረሰቡ ለራሱ ሕልውና ብሎ የሚመሠርተው የጋራ ተቋም ነው። የጋራ ተቋም በመሆኑ ማንም ቢወድም ባይወድም ይታዘዝለታል። የጋራ ተቋም በመሆኑ የሚገነባው በጋራ ትብብር ነው። ጠንካራ ሕዝብ ጠንካራ መንግሥትን ይገነባል፣ ደካማ ሕዝብ ደካማ መንግሥትን ይገነባል። ምክንያቱም መንግሥት የሚወጣው ከማኅበረሰቡ መካከል ስለሆነ። በተለይ የብዙ የተወሳሰቡ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ባሉበት በዚህ ዘመን ጠንካራ የሆነ መንግሥት እንደሚያስፈልግ ያሳያል።
የመንግሥት ዓይነቶች
መንግሥት በአመሠራረቱ (ሥልጣን የሚያገኝበት መንገድ) ፣ በሥልጣን ላይ የሚቆይበት ጊዜና በኀይል አጠቃቀም የተነሣ የተለያየ ስም ይሰጠዋል። በብዛት ዓለም ላይ የተለመዱ የመንግሥት ዓይነቶች
- ንጒሣዊ መንግስት (ሥልጣን የሚሰጠው ከፈጣሪ ነው፣ ወደ ልጅ ይተላለፋል)
- የጥቂት አምባ ገነናዊ መንግሥት (ሥልጣን በኀይል ይገኛል፣ ሌላ ኀይለኛ እስኪመጣ ይቆያል)
- ዴሞክራሲያዊ መንግሥት (ሥልጣን ከሕዝብ ነው፣ በሕግ የተደነገገ ዘመን እስኪያልቅ ያገለግላል)
የኮንሶ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር እንዴት ተዋወቀ?
የኮንሶ ሕዝብ ዘመናዊ የመንግሥት ሥርዐት ጋር ከመተዋወቊ በፊት የራሱን መንግሥታዊ ሥርዐት ፈጥሮ ይተዳደር እንደነበረ ይታወቃል። ይህ የመንግሥት ሥርዐት የሚመስል አስተዳደር ኼልታ ይባላል። ኼልታ የመንግሥትን ሚና ይጫወታል። በማኅበረሰብ መካከል ግጭት እንዳይኖር ይከለክላል፣ አጥፊን ያስጠይቃል፣ ሰላም ያስከብራል፣ ሀብት በሥርዐት እንዲሰራጭና እንዲጠበቅ ያደርጋል። የኼልታ የሥልጣን ዘመን ደግሞ 9 ዓመት ሲሆን ሽግግሩም ሰላማዊ ነው።
ከዘመናዊ መንግሥት ጋር ትውውቅ
የኮንሶ ሕዝብ ከዘመናዊው የመንግሥት ሥርዐት ጋር የተዋወቀው በምንሊክ ዘመን እንደሆነ በተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ተጽፏል። ዐጼ ምንሊክ የግዛት አንድነት ፕሮጀክት በሚፈጽሙበት ጊዜ ወደ ደቡብ ዘምቶ ኮንሶንም ጭምር ወደ ማዕከላዊ መንግሥት እንደጠቀለለ በታሪክ ተጠቅሷል። ወደ ደቡብ የመጣው የምንሊክ የጦር ጀኔራል ልዑልሰገድ እንደሆነ ይታወቃል። የኛ ማኅበረሰብ ያንን ዘመን “ሳፓና ሉሱካቴ” ብሎ ይጠራዋል። የልዑልሰገድ ዘመን ለማለት ነው።
ዘመናዊው መንግሥት ሲመጣ ነባሩን የኼልታ ሥርዐት አጥፍቶ በምትኲ በራሱ ተወካዮች ማስተዳደር ጀመረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኮንሶ ሕዝብ በተለያዩ የመንግሥት ሥርዐቶች ሥር ሲተዳደር ኖሯል። የመጀመሪያዎች ሁለት መንግሥታት ማለትም የምንሊክና የኀይለሥላሴ መንግሥታት ንጉሣዊ መንግሥታት ሲሆኑ በሕዝብ መካከል ያለው መስተጋብር (relation) የገባሪና የጭሰኛ ግንኙነት ነበር።
ከነገሥታቱ ሥርዐት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው መንግሥት የደርግ መንግሥት ሲሆን ባህሪውም ወታደራዊ ነበር። የደርግ መንግሥት ከዚያ በፊት የነበረውን የገባሪና የጭሰኛ ሥርዐት አጥፍቶ መሬትን ለግለሰቦች በማከፋፈሉ አንድ የዕድገት እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ነገር ግን ሥርዐቱ ወታደራዊ በመሆኑ መብቶች በትክክል የሚከበሩበት አልነበረም። የመንግሥት ሥልጣንም ገደብ የለውም። ከሁሉም በላይ የደርግን ሥርዐት አስከፊ ያደረገው ከውስጥም ከውጪ ጠላቶች ጋር ለረጅም ጊዜ እየተዋጋ ስለኖረ በዘመኑ ሰላምና መረጋጋት አለመኖሩ ነው። ሕዝቡም በተራዘመ ጦርነት ተሰላችቷል ተሰላችቶ ነበር።
ደርግን ተከትሎ የመጣው የኢሕአዴግ ሥርዐት ነው። የኢሕአደግ ሥርዓት ከሌሎች የሚለየው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በመሆኑ ነው። ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ስንል ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶንች ሙሉ በሙሉ አክብሮ አስከብሯል ለማለት ሳይሆን ልምምዱን ጀምሮ ነበር ለማለት ነው። በየ 5 ዓመት ምርጫ አለ፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካዮ ይተዳደራል፣ ሕግ መንግሥት ተቀርጿል ወዘተ. . .።
ያለፉት ሥርዐቶች የፈጠሩት የመንግሥት ምስል
መንግሥት ምንድን ነው? የመንግሥት ሚናስ ምን ይመስላል ብለን አንድን አርሶ አደር ብንጠይቅ የሚሰጠን መልስ ከዚህ በፊት ከነበሩት የመንግሥታት ባህሪይ ጋር አስተሳስሮ ሊመልስ ይችላል። ምክንያቱ አርሶ አደር የመማር ዕድል እንዳገኘ ሰው የመንግሥትን ምንነት ከመጽሐፍት አንብቦ ሳይሆን በተግባር የሚያወቀው ነው የዕውቀት ምንጩ።
በነገሥታት ዘመን የነበረው የመንግሥት ሥርዐት የገባርና የጭሰኛ ግንኙነት ስለነበረ የፈጠረው እሳቤ መንግስት ማለት ከሆነ ቦታ መጥቶ ሰዎችን የሚያስገብር ውጫዊ ኀይል ሆኖ ተስሏል። ምክንያቱም በነዚያ ዘመናት የተማረ የአካባቢ ተወላጅ ባለመኖሩ አብዛኞቹ የመንግሥት ተወካዮች ከሌላ ቦታ የሚመጡ ናቸው። ግንኙነታቸውም በስምምነትና በመልካምነት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በኃይልና በማስገደድ ላይ የተመሠረተ ነበር። ሕዝቡ ግብር ይገብራል፣ ለአስገባሪው ነፃ የጉልበት ሥራ ይሠራል፣ አድርግ የተባለውን ያደርጋል። ለምን ብሎ መጠየቅ አይፈቀድም። መንግሥትን ወክለው የሚያስተዳድሩ አካላት ለሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት የተደራጀ ሥርዐት ባለመኖሩ ሕዝብን በድለዋል። ስለዚህ ይኸ ሥርዐት በሕዝብ ውስጥ የሳለው ምስል መንግሥት ማለት የሚያስገብር፣ የሚያስጨንቅ፣ የሚገርፍ ክፉ አባት የሚመስል ሥዕል ነው።
የደርግ ሥርዐት ከነገሥታቱ ሥርዐት በተወሰነ መልኲ የሚሻል ነው፣ በተለይ የገባርና የጭሰኛ ሥርዐትን ከማጥፋት አንጻር። ሆኖም ግን የተደራጀ መንግሥታዊ ተቋማት ባለመኖራቸው፣ የተማረ የአካባቢ ሰው ባለመኖሩ መግንሥት ለሕዝብ ሊሰጠው የሚችለውን አገልግሎት በሙሉ ሰጥቷል ማለት አይቻልም። በተለይ በወቅቱ የነበረው የጦርነት ውጥረት የውትድርና ምልመላ ሕዝብን አማሯል።
የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ ሕዝብ በሙላት የወረዱት በኢሕአዴግ ዘመን ነው ማለት ይቻላል። የኢሕአዴግ ሥርዐት ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድል ስለፈጠረ፣ እንዲሁም ብዙ የአካባቢ ተወላጆች ትምህርት ጨርሰው ሥራ የጀመሩበት ጊዜ በመሆኑ ከነበሩት ሥርዐቶች በአንጻራዊነት የተሻለ የመንግሥት ቊመና የታየበት ጊዜ ነበር። የኢሕአዴግ ሥርዐት ከሌሎች በተሻለ መልኲ ሕዝቡን ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ያሳደገበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን የኢሕአዴግ ሥርዐት ለሕብረተስብ የሰጠው የፖለቲካ ተሳትፎ ዕድል የሚያበረታታ ቢሆንም የአንድ ፓርቲ የበላይነት የተንጸባረቀበት ነበር።

