የሰላም ግንባታና የሰው ልጅ የትግል ታሪክ
ኑሮ ትግል ነው ይላሉ ሰዎች። ሰው ከእናቱ ማኅጸን ወጥቶ ይህችን ዓለም ከተቀላቀለበት ቅጽበት አንሥቶ የመጨረሻ እስትንፋሱን መተንፈስ እስከቻለበት ድረስ በግልም ከሌሎች አቻዎቹ ጋር በመሆንም በሕይወት ግብግብ ውስጥ ነው የሚያልፈው። ትግሉ ሁለት አቅጣጫ አለው። አንደኛው ሰው ከሌላኛው ወገኑ ጋር የሚያደርገው ትግል ነው–የእርስ በርስ ትግል እንለዋለን። ይህም በክርክር፣ በጥል፣ በማሳመን፣ በማመን፣ በግጭትና በጦርነት የሚገለጽ ነው። ታዋቂው ደራሲ ከበደ ሚካኤል ‘ሥልጣኔ ማለት ምንድን ነች’ በሚለው መጽሐፉ የዓለም መንግሥታት በሦስት ሺህ ዘመናት ታሪክ ውስጥ ስምንት ሺህ ጊዜ የወዳጅነት የውል ተፈራርመው ስምንት ሺህ ጊዜ ውሉን አፍርሰው ስምንት ሺ ጊዜ ጦርነት እንደተዋጉ አስቀምጧል[1]።
ሁለተኛው የትግል አቅጣጫ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርገው ግብ ግብ ነው። በሃይማኖትም ሆነ በፍልስፍና ‘ተፈጥሮ’ ለሰው ልጅ ኑሮ የማይመችና ብዙ የመከራ ምንጭ መሆኑ ይታመናል። ስለ ዓለም አፈጣጠር ከጅማረው ጀምሮ የሚያትተው መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጅ ኃጢአት ምክንያት ዓለም እንደተረገመች ያስረዳል፥
“አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፣ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፣ ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።”[2]
ይህ ዓለም ዛሬም አልተቀየረም፣ ይልቁን ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪነቱ እየጨመረ መጣ እንጂ። ምድር እሾህና አሜከላ በማብቀል ብቻ አልተወሰነችም፣ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚባሉት እንደ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መንሸራተት፣ እሳተ ገሞራ፣ ከፍተኛ አውሎ ነፋስ፣ ድርቅ፣መፈናቀል፣ በሽታ፣ ሞት ወዘተ… በተፈጥሮ ውስጥ የሚገለጡ አጥፊ ኀይሎች ናቸው።
የሰው ልጅ ግን ዐቅሙ የፈቀደውን ያህል ተፈጥሮን በራሱ ቊጥጥር ሥር ለማዋል እየታገለ ይገኛል።ዛሬ “ቴክኖሎጂ” ብለን የምንጠራቸው ነገሮች ሁሉ ተፈጥሮን ለሰው እንድትመች ለማድረግ ሲባል የተፈበረኩ ምርቶች ናቸው። በተመሳሳይ መልኲ ብዙ የዲፕሎማሲና የሰላም ስምምነቶች የተፈጠሩት የሰው ልጅ ከሌላኛው ወገኑ ጋር የሚያደርገውን መስተጋብር ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ተብሎ ነው።
ዛሬ በዓለም ላይ የምናያቸው የሥልጣኔ ልዩነቶች የትግሉ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። በተለምዶ የምዕራቡ ዓለም የሚባለው ክፍል በቊሳዊ ሀብትና በሥልጣኔ ደረጃ ከተቀረው ዓለም የተሻለ ሆኖ እናገኘዋለን። በተለይ ከ15ኛ መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ ምዕራባውያን ከተቀረው ዓለም ተለይተው ለብቻቸው ጒዞ የጀመሩበት ዘመን እንደሆን ይታመናል። የጨለማ ዘመን ተብሎ የሚጠራው የመካከለኛው ዘመን ታሪክ የሚነገረን በተለይ በአውሮፓና በተቀረው ዓለም መካከል የሥልጣኔ ልዩነት እንብዛም ነው። ከተጠቀሰው ዘመን ጀምሮ ግን አውሮፓ በብዙ የለውጥ ማዕበል ውስጥ አልፋለች። የሥልጣኔ ዳግም ልደት ወይም ትንሣኤ (Renaissance), ተሐዲሶ (Reformation), አብርሆት (Enlightenment), የኢንዱስትሪ አብዮት ፍንዳታ (Industrial Revolution) ፣ የመረጃ ዘመን ወዘት ሂደቶች ውስጥ ዐልፈዋል። እንደ ሌላው ዓለም በስንጥር መሬት ከመጫር ተነሥተው ዘመናዊ ማሺኖችን ወደማምረት አደጉ፣ በእግር ከሚዳክሩበት ወጥተው እንደ አሞራ አየር እየቀዘፉ መብረር ጅመሩ፣ ባህሩና የብሱን ሁሉ ቧጥጠው ከጨረሱ በኋላ ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ የማይታዩ ዓለማትን ወደ ማሰስ ተሸጋገሩ፣ ጨረቃን በእግራቸው ረገጡ። ባጭሩ ተፈጥሮን በቊጥጥራቸው ሥር አውለዋል ማለት ይቻላል፣ ምንም እንኳን አሁንም ከተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችና ከበዛው የሰው ልጅ ጥበብ በላይ የሆኑ ግዙፍ ችግሮች ቢኖሩም።
የተቀረው ዓለም፣ በተለይ አፍሪካ ግን ከተፈጥሮ ጋር እራሱን አስማምቶ ለመኖር የመረጠ ይመስላል። አንዳንዴ በሰው ጉልበት ያልተገራው የተፈጥሮ ኀይል ጫናውን እያበረታ ለተለያዩ አደጋዎች ሕዝቦቿን ያጋልጣል። ከዚሀ የተነሣ በሽታ፣ ደርቅ፣ ርሃብ፣ ግጭት ወዘት… ከአፍሪካ ጠፍተው የማያውቁ ቤተኛ ችግሮች ሆነው ቀጥለዋል።
ኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኲ ብዙ ሰው ሠራሽም ሆን የተፈጥሮ ችግሮችን ስትጋፈጥ ኖራለች። በጠቅላላው ስንመለከት ግን ተፈጥሮ ካመጣብን ችግሮች ይልቅ እኛ በራሳችን ላይ ያመጣናቸው ችግሮች ይበዛሉ። በተለይ ጦርነቶች ሥልጣኔያችንን ክፉኛ እንደተፈታተነው የሚታወቅ ሐቅ ነው። የሚያሳዝነው ነገር ዛሬም አለመማራችን ነው። እንዳልተማርን የሚያሳየው ሁሉንም ግጭቶች በኀይል መፍታት መሞከራችን ነው።
በቀጠናው ያለን ሕዝቦች የግጭቶችን ዳፋ ከኛ በላይ የሚያውቅ የለም። በግጭቶች ምክንያት ብዙ ዋጋ ከፍለና። የግጭት አዙሪቱ በዚህ ካተገታ ወደ ቀጣዩ ትውልድ መሸጋገሩ አይቀሬ ነው። ስለዚህ ይኸ ትውልድ ሁለት ምርጫ ይኖረዋል። አንደኛው “ግጭት በኛ ይብቃ!” ብሎ ዛሬ ነገ ሳይል፣ ቅድመ ሁኔታዎችን ሳይደረድር ቶሎ ወደ ሰላም ግንባታ መግባት አሊያም እዚህና እዚያ ጫፍ ተወጣጥሮ የግጭቱን አዙሪት በማስቀጠል ለትውልድ ዕዳ ማሸጋገር። መቼስ ቀላሉ መንገድ በግጭቱ መቀጥል ነው፣ እልህ፣ አልሸነፍ ባይነትና የይቅርታ ልብ አለመያዝ የግጭቱ ማስቀጠያ መንገዶች ናቸው። በተቃራኒው ግን ከዚህ በፊት ያልተኬደበትን መንገድ መምረጥ፣ ሰላም የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል የስነ-ልቦና ዝግጅ በማድረግና የመጀመሪያውን ቆራጥ እርምጃ በመራመድ የሰላም ግንባታ ሂደትን ዛሬ መጀመር ይቻላል። በመርህ ደረጃ ማንም ሰው ሰላም እንዲመጣ ይፈልጋል። ከባዱ ውሳኔ ግን እራስን አሸንፎ ሰላም የሚፈልገውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን ነው።
ይቀጥላል. . .
[1] ከበደ ሚካኤል፡ ሥልጣኔ ማለት ምንድንነች (ገጽ. 17)
[2] ኦሪተ ዘፍጥረት ምዕራፍ ፫፥ ቊጥር ፩፯-




